
ፓርቲያችን ብልጽግና በኢህአዴግ ዘመን የነበሩ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችን እና አጋር በሚል ሲጠሩ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶችን በማካተት አቃፊ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሥርዓት የሚገነባ ‹‹ የብልጽግና ፓርቲ›› የሚሰኝ ኅብረ ሀገራዊ ፓርቲ ሆኖ የተቋቋመ ፓርቲ ነው፡፡ የፓርቲያችን ጥቅል ዓላማ የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ነው፡፡ ብልጽግና ስንል ፈርጀ ብዙ ትርጓሜን አዝሎ የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ እና ማኅበራዊ ገጽታ ያለው ነው፡፡
ኢኮኖሚ ብልጽግና ፣ የሕዝቦች መሠረታዊ ፍላጎቶች በተገቢና በዘላቂነት ለማሟላት የሚያስችል ፈጣን እና ሁለንተናዊ ዕድገትን በማስመዝገብ፣ ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትን ያለው ኢኮኖሚ በመገንባት ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥና የህዝቦችን ድህነትና ኋላ ቀርነትን ለመቅረፍ መቻልን ያካተተ ነው፡፡
የፖለቲካ ብልጽግና ስንል ለዴሞክራሲ ባህል ማበብ አስፈላጊ የሆኑ ተቋማትን በመገንባት፣ የሕዝቦች ነጻነትና እኩልነት ተረጋግጦ ሁሉም ኢትዮጵውያን ሰብአዊና ዴሞክሲያዊ መብቶቻቸው ተከብረውላቸው የሚኖሩባትን፣ ኅብረ ሀገራዊ አንድነቷ የተረጋገጠ፣ ፌደራላዊት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ጽኑ መሠረት ላይ ማቆም ነው፡፡
ማኅበራዊ ብልጽግና፤ መልካም ሀገራዊ ወጎችን፣ ዕሴቶችን እና ባህሎችን በማዳበር በሥነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ማፍራት፣ በአካልና በአዕምሮ የዳበረ ጤናማ ዜጋ መፍጠር፣ ከአስከፊ ማኅበራዊ ችግር የተጠበቀ ኅብረተሰብ መገንባት እና በሕዝቦች መካከል አዎንታዊ ሰላም በመፍጠር ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ ማለት ነው፡፡
ክልላችን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እና ዞናችን ምስራቅ ጉራጌ ዞን በ2015 ዓ/ም በመጨረሻው ነሐሴ ወር ላይ ተደራጅው ስራ የጀመሩ ቢሆንም ከተደራጁ ሁለት ዓመት እንኳን ሳይሞላ የክልሉን ብሎም የዞናችንን ህዝብ ተጠቃሚ ማድግ ያስቻሉ በርካታ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራትን ማከናወን የተቻለበት እንዲሁም በቀጣይም በአጭር እና በረጅም ግዜ የላቀ ውጤት በማስመዝገብ የሀገራችን ኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግናን ዕውን ለማድረግ እተጋን እንገኛለን፡፡
ስለሆነም በዞናችን የምትገኙ የፓርቲያችን አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም መላው የዞናችን ህዝቦች የፓርቲያችን የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ዕውን የማድረግ ራዕይ እንዲሳካ ለማስቻል የተመዘገቡ መልካም የልማት ውጤቶች በላቀ ደረጃ ቀጣይነታቸው እንዲረጋገጥና በትጋታችን የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ዕውን ለማድረግ ሁሉም በየተሰማራበት መስክ እንዲተጋና ለውጤት እንዲሰራ አደራ በማለት መልዕክቴን ለማስተላለፍ እወዳለሁ፡፡

